ሴቶችን በእስር የማብቃት የመንግሥት አዲሱ ዕቅድ ይሆን? – ብስራት ወልደሚካኤል
በርግጥ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የስርዓቱን ብልሹ አሰራር የጠቆሙና የተቹ በርካታ ንፁሃን በግፍ እስር እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የእስሩ ሰለባ የሆኑት ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች የኃይማኖት አባቶችና ነፃነት ጠያቂዎች፣ የዩነቨርስቲ ተማሪዎችና አስተማሪዎች፤ኸረ እናት ከነልጇ እና ገበሬዎች ቤት ይቁጠረው፡፡
ባለፈው የግፍ እስር ሰለባ የነበሩት በቀለ ገርባ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህረና የፖለቲካ ፓርቲ አመራር)፣ ርዕዮት ዓለሙ ጋዜጠኛ መምህርት፣ ዘለዓለም ክብረት (የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህርና የዞን 9 በብሎገር)፣ ማኀሌት ፋንታሁን (የዞን 9 ብሎገር)፣ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና ኤዶም ካሳዬ ሲፈቱ ደስ ብሎን ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም በርካታ ንፁሃን በግፍ ታስረው በወህኒ ቤት እየማቀቁ ነውና ሁሉም ሊፈቱ ይገባል ስንል መጠየቃችንን ባናቆምም፤ እስሩ ምልኩን ቀይሮ አዲስ አበባን ጨምሮ በየክልሉ ያለምክንያት የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር ተበራክቷል፡፡
ሰሞኑን እየታሰሩ ካሉት መካከል ደግሞ ከጎንደር አስቴር ስዩም ትገኛለች፡፡ አስቴር ስዩም በያዝነው 2007 ዓ.ም. ከጎንደር ዩኒቨርስቲ በ“Inorganic Chemistry” ማስተርስ ከተመረቀች ገና አንድ ወር እንኳ አልሞላትም፡፡ በጎንደር አካባቢ በኢህአዴግ ምርጫ ቦርድ እስኪፈርስ ድረስ የአንድነት ፓርቲ አባል ነበረች፡፡ ፓርቲው ሲፈርስ ግን ወደትምህርቷ ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት በማድረጓ በክብር ተመርቃለች፡፡
የሚያሳዝነው ይህቺ ወጣት በአንዱ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲ በመምርነት ተመድባ ለመስራት እየተጠባበቀች ሳለ፤ መረፊያሽ የግፈኞች ማጎሪያ ወደሆነው ማዕከላዊ ነው ተብላ እዛ ትገኛለች፡፡ የአስቴር ስዩም ተስፋ በተመረቀችበት(በነገራችን ላይ በሀገራችን በዘርፉ ብዙ ባለሙያ የለም) ሙያ በምትመደብበት ዩኒቨርስቲ መምህር ሆና ማገልገል ቢሆንም ፤ባለፈው ሳምንት ምረቃዋን አጣጥማ ሳትጨርስ ከምትኖርበት ጎንደር ከተማ በደህንነቶች ታፍና አዲስ አበባ ማዕከላዊ መምጣቷ ታውቋል፡፡
ስለዚህ ይህንን አዲሱ ሴቶችን በእስር የማብቃት የሁለተኛው ዙር የመንግሥት የዕድገትና እመርታዊ ዕቅድ (GTP II) ይሆን?
አሊያም ሴቶችን እናንተ ተማሩ እኛ እናስራለን የሚል ቀጣይ ዕቅድ ይሆን…?
ኮካዎች እዚህ ላይ የምታውቁት ነገር ካላችሁ ጀባ በሉን እስኪ!