ምርጫ የሰላማዊ ትግል ስልት ሳይሆን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ ነው! ዮናታን ተስፋዬ ረጋሳ ከሰማያዊ ፓርቲ

(ይህ የግሌ አስተያየት ነው!)

ምርጫ ካልተገባ ሌላኛው አማራጭ ትጥቅ ትግል ብቻ ነው ያለው ማነው? ሲጀመርስ ምርጫ የዲሞክራሲ መገለጫ ነው እንጂ ከመቼ ወዲህ ነው የሰላማዊ ትግል አካል ሊሆን የሚችለው፡፡ ሰላማዊ ትግል ዲሞክራሲ በሌለበት የሚደረግ ትግል ከሆነ ዘንዳ የዴሞክራሲ መገለጫ የሆነው ምርጫ ሰላማዊ ትግል ነው ማለትስ ምን ማለት ነው?

ሰላማዊ ትግል እኮ ሰላማዊ ትግል ያስባለው መሳሪያ የሚያስነሳ ጭቆና መኖሩ ነው፡፡
ግልፅ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ
በምርጫ የሚደረግ ትግል ህዝቡ የስልጣኑ ባለቤት በሆነበት ሀገር እንጂ ሁሉም ነገር በአገዛዙ መዳፍ ስር በሆነበት ሁናቴ አይደለም፡፡

ሰላማዊ ትግል ዲሞክራሲ ጨርሶውኑ በሌለበትና እየሞቱ ማሸነፍ ግድ የሆነበት የትግል አካሄድ ነው፡፡
የትጥቅ ትግልም ዲሞክራሲ ፈፅሞ በሌለበት ሀገር ውስጥ እየገደሉም እየሞቱም ለማሸነፍ የሚደረግ ትግል ነው፡፡

ከዚህ በመነሳት
1- አሁን ባለንበት ሁናቴ ምርጫ ማካሄድ የዴሞክራሲ ሂደት ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ማለት ሲሆን
2- ኢህአዲግን በፈቃዳችን እንደ መንግሰት እውቅና መስጠት ነው

ስለዚህ፡- ትግሉ ሰለማዊ ትግል ነው የምንለው ምርጫ ማድረግ የሚቻልበትን ምህዳር መፍጠር፤ ህዝቡን የስልጣኑ ባለቤት ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በመሁኑ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ማቸውንም የፖለቲካ ስራ በነፃነት መስራት በማይቻልበት ሁናቴ ነፃነት እንዲኖር መታገል ከሁሉ በፊት መሆን ያለበት ትግል ነው፡፡ ይህ ትግል በባህሪይው እልህ አስጨራሽ፣ ተስፋ አስቆራጭ፣ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል … ፍሬው ግን ዘላቂና እጅግ አስደሳች ነው፡፡ ለዛ ነው ደጋግመን ህይወታችንንም ቢሆን እስከመስጠት ድረስ ፍፁም ሰላማዊ ሆነን እንታገላለን የምንለው፡፡

ሰለማዊ ትግል ከነፍጥ ትግል የሚለየውም በዚሁ ባህሪይው ነው፡፡ በመውደቅ በመነሳት ውስጥ ማሸነፍ፤ ሳይገድሉ በመሞት ማሸነፍ፡፡ ይህ መንገድ በምርጫ ከሚደረግ የስልጣን ትግልም ሆነ መሳሪያ አንስተው በሀይል ስልጣን ለመያዝ ከሚደረግ ትግል ፍፁም የተለየ ነው፡፡ ነፃነት ትግል ይፈልጋል፡፡ ፍፁም ሰላማዊ ሆነን እናሸንፋለን!
Image