አቧራውን ለማጥራት ነፃነት ለምርጫው ቅድመ ሁናቴ ነው!!!

Eyasped Tesfaye
ይህን ሁለት ቀን በማህበራዊ ድህረ-ገፆች ላይ በትብብሩ እና በፓርቲዬ ላይ እየተናፈሰ ያለውን አቧራ ማጥራት ግዴታ ስለሆነብኝ የሚከተለውን ፅፊያለሁ፡፡ ልቦና ያለው ልብ ይበል፡፡
ሰማያዊ እና ትብብሩ የምርጫ ምልክት ወስደዋል እንዲሁም ደግሞ የትብብሩ ዋና ፀሀፊ ያለምንም ቅድመ ሁናቴ በምርጫው እንደሚሳተፉ በፌስቡክ ገፃቸው መግለጫ ሰጥተዋል በሚል ከተለያዩ አቅጣጫዋች የተለያዩ ድንጋዮች እየተወረወሩ ነው፡፡ የዚህ ነገር መነሾ ለእኔ ሁለት ምክንያት ያለው ይመስለኛል፡፡
1ኛ፡- ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንድነት ፓርቲ ያለምንም ቅድመ ሁናቴ በምርጫው እሳተፋለሁ ማለቱን ተንተርሶ በሶሻል ሚዲያው ላይ አንድነት ፓርቲን የሚያጥላሉ ፅሁፎች በርክተው ነበር፡፡ አሁን እንደገባኝ ከሆነ ወንድሜ አስራት አብርሀምን ጨምሮ የተወሰኑ ሰዎች አንድነት ላይ ዘመቻውን የከፈቱት ሰማያዊዎች ናቸው የሚል ግንዛቤ ወስደው የነበረ ሲሆን የአሁኑ ፅሁፋቸው የመልስ ምት እንደሚሉት አይነት መሆኑ ነው፡፡ በወቅቱ ግን ወዳጄ ዮናታን ተስፋዬ(የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ) በፌስቡክ ገፁ ላይ ከዚህ በታች በፎቶ ያያዝኩትን ፅሁፍ ፅፎ ነበር፡፡ ሰሚ አላገኘም እንጂ፡፡
2ኛ፡- የሰሞኑን አቧራ ያስነሱት ሰዎች ምርጫውን ያለምንም ቅድመሁናቴ እንሳተፋለን ብሎ መግለጫ በመስጠት እና ‹ነፃነት ለፍትሀዊ ምርጫ› ብሎ ምርጫው ፍትሀዊ እንዲሆን በመታገል መካከል ያለውን ልዩነት በቅጡ ያልተገነዘቡ ናቸው፡፡
ማብራሪያ፡-
ሰማያዊ ፓርቲና ሌሎች ስምንት ፓርቲዎች በጋራ በመሆን ነፃነት ለፍትሀዊ ምርጫ የሚል እንቅስቃሴ እያደረጉ እናዳለ ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ የዚህን እንቅስቃሴ ስያሜ እንኳን በቅጡ ብናየው ሁለት ነገሮችን እንገነዘባለን፡፡ የመጀመሪያው ነገር ነፃነት ሳይኖር ምርጫ ሊኖር አይችልም ስለዚህም ነፃነት የምርጫ ቅድመሁናቴ ነው የሚል ሀሳብ የያዘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በነፃነት የሚደረግ ምርጫ እንዲኖር ትግል እንደሚደረግ አመላካች ነው፡፡
ከፊታችን የሚደረገው የ2007ቱ ምርጫ ነፃና ፍትሀዊ እንዲሆን ታግዬ ነፃ ሲሆን እሳተፋለሁ ማለት እና ያለምንም ቅድመ ሁናቴ በምርጫ እሳተፋለሁ ብሎ መግለጫ መስጠት ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ ለነገሩ የዛሬው ጫጫታ ከጀርባው ሌላ ተንኮል እንዳለው አንዱ ማሳያ የትብብሩ ፀሀፊ የሆኑት አቶ ግርማ ከዛሬ 10 ቀን በፊት ከግርማ ካሳ ጋር በኮመንት ሲከራከሩ ኮመንት ያደረጉትን ነገር አዲስ መግለጫ እንደሰጡ በማስመሰል ‹‹ሰማያዊ ያለምንም ቅድመ ሁናቴ በምርጫው እንደሚሳተፍ ገለፀ›› ብሎ ዜና መስራቱ በራሱ የጤነኝነት አይመስልም፡፡ ምናልባትም ሰማያዊም ሆነ ትብብሩ ነፃነት ከሌለ ምርጫ የለም በሚል በያዙት ጠንኳራ አቋም ምክንያት ያገኙትን ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ለማሳጣት የታለመም ይመስላል፡፡
ሰማያዊ የምርጫ ምልክት ወሰደ ማለትስ በምርጫው ውስጥ ያለምንም ቅድመሁናቴ በምርጫው እሳተፋለሁ ብሎ መግለጫ ሰጠ ወይም ወሰነ ማለት የሚሆነው እንዴት ነው??? ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ 2007ትን ከወዲሁ ቦይኮት ማድረጉን ቢገልፅ እና ከሂደቱም ራሱን ቢያገል፤ በአንፃሩም ሰማያዊ እና ትብብሩ ነፃነት ለፍትሀዊ ምርጫ በሚል እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ ውጤት ቢያመጣና ምርጫው ነፃ ቢሆን ማን በጠረገው መንገድ ማን ሊሄድ ነው??? ይህ የነፃነት ለፍትሀዊ ምርጫ የሚለው ትግል እኮ ቢያፈራ ፍሬውን ለመሰብሰብ በሂደቱ ውስጥ መቆየት ግድ ነው፡፡
አንድነት ያለምንም ቅድመሁናቴ በምርጫው እሳተፋለሁ ብሎ መግለጫ መስጠቱን አልቃወምም፡፡ አባላቶቼን ከወዲሁ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ይረዳኛል ብሎ ይሆናልና፡፡ ልክ እንደዚሁም ሁሉ ሌላውም የእኛን አቋም እንዲያከብርልን እሻለሁ፡፡ ሰማያዊ እና ትብብሩ ምርጫ የሚኖረው ነፃነት ሲኖር ነውና ነፃነት ለፍትሀዊ ምርጫ ብለው እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አዲስ ነገር የለም! አይኖርምም!!!