የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) = አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የአቋም መግለጫ
ፓርቲያችን አንድነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ በሠላማዊ ትግል ትንቅንቅ ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች ግንባር ቀደሙ ነው!
በትግሉ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልዕልና እየተጋ ያለው ፓርቲያችን በየጊዜው በሚገጥሙት መሠናክሎች ከመዳከም ይልቅ እየጠነከረ፤ ውስጣዊ ዴሞክራሲው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጎለበተ የመጣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄ በአስተማማኝ መንገድ ለመመለስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቁርጠኛ አባላትን ያፈራ በመሆኑ ኩራታችን ከፍ ያለ ነው፡፡
አንድነት በ2ዐዐ7 ዓ.ም. በሚካሄደው ምርጫ አሸናፊ ኃይል ሆኖ ለመውጣት መሠረተ ሠፊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህ ሠፊ እንቅስቃሴያችን ምክንያትም ገዢው ፓርቲ በአባላትና አመራሮቻችን ላይ ከፍተኛ የሆነ የእስር፣ የማሳደድና የማጥፋት ሥራ እየሰራ ቢሆንም ፓርቲያችን ይህንን ሁሉ ጫና በመቋቋም አሁንም በሠላማዊ ትግል የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ በቁርጠኝነት ቆሟል፡፡
ለዚህ ቁርጠኝነታችንና ፓርቲያችን ስላለው መሠረተ ሠፊ አደረጃጀት ከዚህ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በላይ ምስክር የለም፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ጉባኤ ለማድረግ ችለናል፡፡ ይሄ ፓርቲያችን የደረሰበትን እድገት የሚጠቁም ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ፓርቲዎችም አርአያ ለመሆን የሚበቃ ነው፡፡
እኛ የእዚህ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ አባላትም በዛሬው እለት ባደረግነው አስቸኳይ ስብሰባም የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፈናል፡፡
1. የፓርቲው ብ/ም/ቤት የቀድሞው የፓርቲው ፕሬዚደንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ብ/ም/ቤቱ ባለው የጠቅላላ ጉባኤ ውክልና መሠረት ያካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ተገቢና ሕገ-ደንባዊ መሆኑን አረጋግጦ አቶ በላይ ፍቃዱን እስከሚቀጥለው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ፕሬዚደንት እንዲሆኑ በከፍተኛ ድምጽ ወስነናል፡፡
2. በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ ከብ/ም/ቦርድ የሚፈለጉ ማብራሪያዎችን እና ሃሳቦች ተከትሎ ጠቅላላ ጉባኤው የተወሰኑ ማሻሽያዎች አድርጓል፡፡
3. መድረክን በተመለተ በፓርቲያችን ላይ የጣለውን ሁለተኛ እገዳ ተከትሎ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ በወሰነው መሠረት ብ/ም/ቤቱ ከመድረክ እንዲወጣ የወሰነውን ውሳኔ ተገቢ ሆኖ ስላገኘው በከፍተኛ ድጋፍ አፀድቋል፡፡
4. ገዢው ፓርቲ ህገ መንግሥቱን በመጣስ በእየእስር ቤቱ ያጎራቸውን የዴሞክራሲ አርበኞች በአስቸኳይ እንዲፈታ ጉባኤው አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
5. የዜጎችን በነፃ የመደራጀት ነፃ አመለካከታቸውን በአምባገነንነት በማፈን ያሰራቸውን የነፃነት አርበኞች ፖለቲከኞች ፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች፣ የቤተ እምነት መሪዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እየጠየቅን መንግሥት በሩን ለብሔራዊ ውይይት ክፍት እንዲያደርግ ጉባኤው ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
6. የተቀማነውን ነፃነታችንን በድምፃችን ለማስከበር ‹2ዐዐ7 ለለውጥ› የሚል የህዝባዊ ንቅናቄ ዘመቻ አንድነት በዛሬው እለት ጠቅላላ ጉባኤው አውጇል፡፡ ስለዚህ መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫው በንቃት በመሳተፍ በምርጫ ካርዱ ነፃነቱን እንዲያስከብር አንድነት ፓርቲ ጥሪውን ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ በአክብሮት ያስተላልፋል፡፡
በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ነፃነታችንን እናስከብር!
የአንድነት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ታህሣሥ 3/2ዐዐ7 ዓ.ም
አዲስ አበባ