አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ተጀመረ – UPDATE
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የጠራው ጠቅላላ ጉባኤ የተጀመረ ሲሆን ተሳታፊዎች የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት አረንጓዴ ፤የአዲስ አበባ ምክር ቤት ቢጫ፤ የክልል ዞን ተወካዮች ቀይ ቲሸርቶችን በመልበስ ለጉባኤው ድምቀት ሰጥተውታል፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አርብ (03/04/07) ጠቅላላ ጉባኤውን ያደርጋል፡፡ ፓርቲው ከዚህ ቀደም በታህሳስ 19/20/2007 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን አመት ሳይሞላ ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ለምን እንዳስፈለገ የጉባኤ ጠሪ ኮሚቴ የሆኑትን አቶ አስራት ጣሴን አነጋግረን ነበር፡፡ አቶ አስራት እንዳብራሩት በታህሳስ 2006 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው ጠቅላላ ጉባኤ ምርጫ ቦርድ ማብራሪያ ጠይቆ ነበር፡፡ አቶ አስራት በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ 573/2000 መሰረት ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት ማብራሪያ መጠየቅ እንደሚችል ገልፀው በሀምሌ 25 ቀን 2006 ዓ.ም በፃፈው ባለ ሶስት ገፅ ደብዳቤ ዘጠኝ ማብራሪያ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን አቅርቦ ነበር፡፡
አንድነት ፓርቲ በበኩሉ ሀምሌ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ለተጠየቁት ጥያቄዎች ማብራሪያ ላከ፡፡ ከተላከው ማብራሪያ በመነሳት ምርጫ ቦርድ ጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም ጥያቄዎቹን ወደ 6 ዝቅ አደረገ፡፡ ፓርቲው በበኩሉ ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ለተጠየቁት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጠ፡፡ ከዚያ በመቀጠል ምርጫ ቦርድ ህዳር 10 ቀን 2007 ዓ.ም ሶስት ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን ጥያቄዎች ያቀረበ ሲሆን ፓርቲውም ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም ማብራሪያ ሰጥቶባቸዋል፡፡
ለአሁኑ ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት ምክንያት የሆነው ህዳር 19 ቀን 2007 ዓ.ም ወደ አንድ ወርዶ በምርጫ ቦርድ የቀረበው ጥያቄ ነው፤ ፓርቲው የጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊ ቁጥሩን እንዲገልፅ የተጠየቀበት፤ ፓርቲው የጠቅላላ ጉባኤ ቁጥሩ 320 መሆኑን ገለፀለት፡፡ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ይህ ቁጥር ታህሳስ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም በተደረገው ጉባኤ በተሻሻለው በደንብ ባለመካተቱ ተካቶ ይቅረብልኝ ሲል ጠየቀ፡፡ በዚህ ሁኔታ በፓርቲው ደንብ መሰረት የጠቅላላ ጉባኤ ቁጥር መወሰን የሚችለው ራሱ ጉባኤው በመሆኑ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት እንዳስፈለገ አቶ አስራት ጣሴ ገልፀውልናል፡፡
አቶ አስራት በመጨረሻ ባስቀመጡት ሀሳብ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ሲደርስ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ መጠየቁ እኛን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት ቢሆንም ህጋዊ መሰረት ግን አልነበረውም ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በደንቡ ላይ የጠቅላላ ጉባኤውን ተሳታፊ ቁጥር የወሰነው ብቸኛው ፓርቲ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ብቻ እንደሆነ ታውቋል፡፡
