የህወሓት ኢህአደግ የማፅዳት ስትራተጂ ሲጋለጥ

ከአስገደ ገ/ስላሴ
Image
የህወሓት መሪዎች ከ40 ዓመት በፊት ጀምረው ለህወሓት መሪዎች የሚቃወም ወይም ደግሞ ከነሱ የበለጠ ሃሳብ የሚያመነጭ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ በውስጣቸው ሳይቀር ካለ ለሚፈልጉትን ዓላማቸው ያሰጋናል የሚሉትን ሁሉ በጠላትነት ደረጃ በማስቀመጥ ያላቸው ልዩነት በክብ ጠረቤዛ በውይይት በመፍታት ፈንታ በኢትዮዽያ የነበሩ የደርግ ተቃዋሚዎች ኋላም ለህወሓት መሪዎች ለተቃዋሚ ኃይሎች ጦርነት በማወጅ ከሁሉም ጋር በጦርነት ፈቱት::

በጦርነት ከጠፉ ፓርቲዎች ለመጥቀስ ለትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት TELF ጋድሎ ሓርነት ትግራይ ጠረናፊት ኮሚቴ የኢትዮዽያ ዲሞክራሲያዊ ሕብረት (ኢዲህ) ለኢህአፓ ለዓፋር ነፃ አውጪ ግንባር (ጉጉመ) ለኦነግ ለአብነግ በደቡብ ለነበሩ ፓርቲዎች ለቅንጂትና ለሌሎች አጠፉ::

ይህ የማጽዳት ስትራተጂ በመቀጠል ለህወሓት ኢህአደግ የሙጡኝ ብሎ በስልጣን ለዘልዓለም ለመኖር እንቅፋት ሊፈጥሩልኝ ናቸው ብሎ የሚገምታቸው የመድረክ አባል ፓርቲ የነበሩ እነ አንዳለም አራጌና ሌሎችም በቅርብ ደግሞ የአንድነት የሰማያዊ ፓርቲ የሚኢአድ የኦሮሞ ፓርቲዎች የዓረና ፓርቲ አሸባሪ ናቸው በማለት ለ2007 ዓ/ም ሃገራዊ ምርጫ ሾልከው ገብተው በፓርላማ መድረክ ሊገቡ ይችላሉ ብሎ የሚገምታቸው ጦርነት ባያውጅም ከጦርነት የባሰ ሽብርተኝነትን በመፍጠር በመላው የሃገራችን ክልሎች የሚገኙ የሰላም ታጋይ ወጣት ሙሁራኖች ጋዜጠኞች የማሕበራዊ ድህረ ገፆች ፀሐፊዎች በቃሊቲና በቅሊንቶ ወህኒ ቤቶችና በማእከላዊ የደህንነት ምርመራ አጉሮዋቸው እያሰቃያቸው ይገኛሉ:: ይህ ተግባር ከ 4 ወር በፊት በአንድነት በሰማያዊ በዓረና ፓርቲዎች ወጣት የሙሁራን አመራር ታስረዋል ተገርፈዋል ተመሳሳይ እርምጃ ወጣት ሙሁራኖች ቅስማቸው እንዲሰበር ለማድረግ ነው:: እንደዚህ ዓይነት ተግባር የሚያሳየው የህወሓት መሪዎች ለ40 ዓመታት ይዘውት የመጡ የሥራ ልምድ ስልጣንህ እድሜ እንዲኖረው እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚባለው አስቀድመህ ማፅዳት ከሚል ፀረዲሞክራሲ ስትራተጂ የመነጨ ፖሊሲ ነው:: እንደዚህ ዓይነት አሰራር የህወሓት መሪዎች መለያ ባህረያቸው ነው::

ኢህአደግ በዚሁ በ40 ዓሙቱ ይከተለው ያለው አሰራርም ለመጪው የ2007 ዓ/ም ምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖው ለማሸነፍ ወይም ደግሞ ብዙ ተቃዋሚ አባላት ወደ ፓርላማ ሊገቡ ይችላሉ ብሎ ታሳቢ በማድረግ የህዝብ ነባራዊ ሁኔታ ስልአሰጋው ሃቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው የሚሉዋቸው የነ አንድነት ሰማያዊ ፓርቲ መኢአድ መድረክ የወጣት አመራርና ጠንካራ አባላት ያሉዋቸው ናቸው::

ስለዚህ እነዚህ ፓርቲዎች ጠንካረዎች በመሆናቸው አስቀድመን ማፅዳት አለብን አሉ:: ለዚሁ እርምጃ መውሰድ ሽፋን ይሆናቸው ዘንድ ወንጀል እየለጠፉ ደረቅ ወንጀል ፈፅመዋል፣ ሕገ መንግስት ጥሰዋል፣ አሸባሪዎች ናቸው በማለት የኢትዮዽያ ወህኒ ቤቶች በወጣት ፖለቲከኞች ተመልተዋል::

የህወሓት መሪዎችና አጋሮቻቸው በሰላም ታጋዮች ላይ እየወሰዱ ያሉ እርምጃ የህዝብ ፍላጎት በፋሺስታዊ እርምጃ በመግደል በማሰር በመግረፍ እንደማይቀለበስ ደርግ የሃገራችን ሃብትና የሰው ኃይል ወደ ጦርነትና ጭፍጨፋ አሰማርቶ የአፍሪካ ጎብለል እየተባለለት በህዝቦች የተባበረ ክንድ እንደተንኮታኮተ የቅርብ ጊዜ ትዝታ እያላቸው ተመሳሳይ የደርግን ፋሺስታዊ ተግባር ተከትለው ሁለተኛ ስህተት መፈፀማቸው አሳዛኝ ክስተት ነው::

እነዚህ ሰዎች 40 ዓመት ሙሉ በዲሞክራሲ ኃይሎች ያደረሱትን ፀረዲሞክራሲ የማፅዳት ዘመቻ ቢታቀቡ ለራሳቸውና ለህዝባችን ይበጃል::