ለተቃዋሚዎች…….ለድክመታችን ሁሉ ኢህአዴግ ተጠያቂ አይሆንም!!! ጋሻው መርሻ
በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ታሪክ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በህገ መንግስት እውቅና ያገኘውና በይፋ ፓርቲ መመስረት የተቻለው በኢህአዴግ ዘመን ነው፡፡ ይህ መቸም እንደ ጅምር ሊያስመሰግን የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ምንም እንኳ ኢህአዲግ ለነፍሱ ብሎ ባያደርገውም፡፡ ሁኔታዎች አስገድደውት ያደረገው እንደሆነ ቢታወቅም በይፋ መደራጀት መቻልን እንደ ትልቅ ለውጥ ነው የምወስደው፡፡
ቁም ነገሩ ግን ኢህአዲግ የፈቀደልንን ህገ መንግስታዊ (ከጫካ ስለሆነ የመጣው ያለመፍቀድ እድልም ነበረው) የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ተጠቅመን ለውጥ ለማምጣት ተንቀሳቅሰናል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ለእኔ መልሱ አይደለም የሚል ይሆናል፡፡ ከአዛውንቱ ዶክተር አስራት ወልደዬስ በቀር አንድም እንኳ ህዝብ አስተባብሮ መሬት ያረፈ ትግል ያደረገ እና ኢህአዲግን የተገዳደረ ፓርቲ ፈጽሞ የለም፡፡ ከጠብ-መንጃ ጋር ፊት ለፊት በባዶ እጅ የተጋፈጡት ቆፍጣናው ምሁር አስራት ውልደዬስ እድሜያቸውና ክብራቸውን በማይመጥን ሁኔታ ለእስር ተዳርገው ለሞት ቢበቁም ከእርሳቸው በኋላ ለምልክት እንኳ የተንቀሳቀሰ የፓርቲ መሪም ሆነ ፓርቲ አላየሁም፡፡
ለዚህም እንደ ማሳያ የሚሆነው አንድም እንኳ የፓርቲ መሪ ለእስርም ሆነ ለሞት ሲዳረግ ታይቶ አለመታቁ ነው፡፡ በአካልም ሆነ በመንፈስ አንዳች ጉዳት ደርሶባቸው አለማወቁ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የግድ ለምን አልታሰሩም ወይም አልሞቱም የሚል መንቻካ ሀሳብ ለማንሳት ሳይሆን ከኢህአዲግ አምባገነንነት አንጻር ምንም አይነት እርምጃ ያለመውሰዱ የመሪዎቹን ልክ ያሳያል ለማለት ነው፡፡ ሁሉንም የግፍ ገፈት የሚጨልጡት አባላትና ዜጋው ነው፡፡ ቆፍጣናዋን እንስት ብርቱካን ሚዴቅሳን ግን መርሳት ከቶ አይቻልም፡፡
በኢህአዲግ ክፍተት ወይም እንዝላልነት በአጋጣሚ የተገኘው የ1997 ዓ.ም ተሞክሮም ቢሆን በፖለቲከኞች ልፋት ያልመጣ መሆኑ ለክርክር የሚቀርብ አይደለም፡፡ የመለስ ዜናዊ ‹‹እንከን አልባ ምርጫ እንደርጋለን›› ፉከራን ተከትሎ ገርበብ ያውን በር ነጻነት የተጠማው ህዝብ በርግዶት ከመግባቱ በቀር ይህን አስተዋጽኦ አደርጌያለው የሚል ካለ ለክርክር ፈቃደኛ ነኝ፡፡
ምን ይሻል???
እስካሁን የነበረውን ‹‹የእናቴ ቀሚስ ጠለፈኝ›› ማስተባበያ ወደ ጎን ብለን ህዝቡ ድረስ በመውረድ ማደራጀት፤ የነጻነትን ጣዕም እንዲያውቅ ማንቃት፤ ዲሞክራሲን በተግባር ማለማመድ፤ ህዝቡ የሥነ ልቦና ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለውድቀታችን ሁሉ ኢህአዲግን መክሰስ ግን እንደ ቋንጣ የደረቀና አዋጭ ቢዝነስ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ለፖለቲካችን መበላሸት ኢህአዲግ ሰፊ መዳፍ የለውም የሚል የሞኝ አስተሳሰብ የለኝም፡፡ የእኔ መከራከሪያ የኢህአዲግ ባህሪ የታወቀ ስለሆነ እርሱን ወደ ጎን ትተን እና እረስተን ህዝቡ ጋር መድረስና ህዝባችን ማንቃት የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም የነቃ ህዝብ ለጭቆና ስለማይች፡፡ በተቃራኒው ያልሰለጠነና ያልነቃ ህዝብ ‹‹ቢጭኑት አህያ ቢጋቡት ፈረስ›› ከመሆን አያልፍምና፡፡
‹‹መንግስት የቆመጠው ቆማጣ አይባልም›› ብሎ የሚተርትን ህዝብ መንግስት መቁመጥ መብቱ አለመሆኑን ማስረዳት ይኖርብናል፡፡ በተቃራኒው ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን የበላይነት አንጽሮ መንገርና ሀሳብ ማስታጠቅ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ የሀገራችን ፖለቲከኞች ኢህአዲግን ከመክሰስ እና ሰሞነኛ ነገር ከማራገብ ያለፈ ስር ነቀል ለውጥ የምንፈልግ አይመስለኝም፡፡
‹‹ኢህአዲግ ገዳይ ነው፤ ኢህአዲግ ያስራል ፤ ያፈናቅላል፤ ያሰድዳል፤ የመንግስትን በጀት ለድርጅት ይጠቀማል፤ ይዋሻል…..ብላ ብላ ከሚል ማላዘን ያለፈ ተጨባጭ አማራጭ የለንም፡፡ አለን የምንለው እንኳ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ አይደለም ሀገርን ያክል ትልቅ ነገር ይቅርና መንደር ለመምራት የሚያስችል አቅም ያለው ፓርቲ ማግኘት ጨረቃ ላይ እንደመውጣት ያለ ከባድ ነው፡፡
‹‹የኢህአዲግ የትምህርት ፖሊሲ የተሳሳተ ነው›› የሚል ተቃዋሚ አማራጭ የማቅረብ ግዴታ አይኖርበትም፡፡ እውነታ ግን ባ ተቃውሞ ብቻ ነው፡፡ የእያንዳንዱን ፓርቲ ገመና ቀርባችሁ ስታዩት ከበርሜል ጩኸት አይለይም፡፡ ባዶ ‹‹የእንዲህ ሆነብን›› ጩኸት!! ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት ለውጥ ማምጣት ይቻለል?? በነገራችን ላይ ‹‹ኢዴፓ›› መስተካከል ያለበት እንዳለ ሆኖ ማንም ፓርቲ ሊስተካከለው የማይችል ዝርዝር የትንታኔ ሰነድ ባለቤት ነው፡፡
መፍትሄው
መፍትሄው እራሳቸውን በሸንበቆ አጥር ከልለው በጸጉር ስንጠቃ አባዜ የተበታተኑ ፓርቲዎችን ወደ አንድ ጎራ እንዲፈሱ በማድረግ ግዙፍ የሆነ እና አማራጮችን ማቅረብ የሚችል የተቃውሞ ጎራ መፍጠር ብቻ ነው፡፡ ደግሞም ይህን ለማድረግ የሚያግድ አንዳች እንኳ ምክንያት የለም፡፡ ምን አልባት እንደ ዘመነ መሳፍንት ሁሉ በዬ መንደሩ አለቃ ሆነው የከረሙት የፓርቲ አመራሮች ይህ እንዳይሆን አይታገሉም ማለት አይደለም፡፡
ነገር ግን ኢህአዲግን ከመታገላችን በፊት እነዚህን ‹‹የመንደር አውራዎች›› ልክ ማስገባት ለነገ የማይባል ስራ መሆን ይኖርበታል፡፡ መነጋገሪያችን መሆን ያለበትም ፍትህ የተጠማውን ህዝባችን መታደግ የሚችል ፋና ወጊ ፓርቲ እንዴት መመስረት ይቻላል የሚል መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ ለዛሬ እንጅ ለነገ መባል አይገባውም፡፡
በተባበረ ክንድ ወደ ነጻነት የምንጓዝበት ቀን ሩቅ አይሆንም!!
…………….እናቸንፋለን……!!!