የኢትዮጵያ ህዝብ በፖለቲካ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ መስክ ቁም ስቅሉን እያየ ነው።
አስፈላጊውን ግብር እና ቀረጥ እስከከፈልን ድረስ የጸጥታ አስከባሪዎች ስራ እና የህገመንግስቱ ትርጉም ይነገረን::
ምንሊክ ሳልሳዊ ፦ዞር ብለን ካለፍነው የኢትዮጵያ የፍትህ ታሪክ እንዳነበብነው ከወላጆቻችን እና ከቅርብ መካሪዎቻችን እንደሰማነው የፊውዳሉ ንጉሳዊ ስርኣትም ይሁን የወታደራዊው ደርግ አገዛዞች በፍትህ አካላት ላይ ፖለቲካን ተገን አድርገው ፍትህን ያዛቡበት ቦታ አልተጠቀሰም :: የፖለቲካ ባላንጣዎቻቸውን ፍትህን ለሃሰት ተጠቅመው ማስረጃ ፈብርከው በየእስር ቤቱ በህገወጥነት አላጎሩም:: እነዚህ ሁለት ሰው በላ እና አራጅ መንግስታቶች የማንንም ህዝብ መብት በፍትህ ስም አልተጋፉም በፍርድ ቤቶች ላይ አዛዥ አልሆኑም::
ፍትህ ካለ ሰላም አለ:: ፍትህ ካለ የተደበላለቁ ስሜቶች ራሳቸውን ይገዛሉ:: ፍትህ ካለ የበላይ አካላት ለህዝብ ይታዘዛል:: ፍትህ ካለ ዲሞክራሲ ይጎለብታል:: ፍትህ ካለ ማንኛውም ሰው በነጻነት ይዘዋወራል:: ፍትህ ካለ እያንዳንዱ ሰው የራሱን መብት ያቃል;የሌላውንም ያከብራል … ፍትህ ካለ የጸጥታ ሃይሎች የወጡበትን አብራክ አይረግጡም የእናት ሃገር ማህጸንን አያደሙም ህዝብን አያስለቅሱም ወዘተ….. ስለዚህ ፍትህ ላይ ማተኮር የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ነው::
አሁን ግን እያየነው ያለው ፍትህ ከሁለቱ መንግስታት በተለየ ሁኔታ ህዝብን በፖለቲካ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ መስክ ቁም ስቅሉን እያሳየው ነው:: የሃገሪቱ ህገ መንግስት ከሚፈቅደው ውጪ እና ውጪ በፖለቲካ መስክ የአይናቸው ቀለም ያላማረ ተቃዋሚዎች ይደበደባሉ ይታሰራሉ ይገረፋሉ በፍርድ ቤት በሃሰት መረጃ ከህግ ትእዛዛት ውጭ የረዥም አመት እስር ይከናነባሉ:: እንደ መንግስት ባለስልጣናት ሳይሰርቁ ደፋ ቀና ብለው ያፈሩት ንብረት ይወረሳል::ከዛም አለፍ ካለ በአደባባይ ይረሸናሉ:: በደህንነት ሃይሎች ይገደላሉ:: ይህ የሚያሳየው የጸጥታ ሃይሎች ከህግ በላይ ሆነው ፍትህን መግደላቸው ነው:: የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳይንቀሳቀሱ የጸጥታ ሃይሎች እንቅፋት ከመሆን አልፈው ወደ አንድ ፓርቲ ያደላ ኮንትሮባንዳዊ ፖለቲካ እየፈጸሙ ነው:: በፓርቲዎች ላይ ወከባ እየደረሰ ነው:: የጸጥታ ሃይሎች ደሞዝ የሚከፈላቸው ከህዝብ ኪስ ሆኖ ሳለ የሚያዋክቡት እና ፍትህ የሚያጎድሉበት የሚያስለቅሱት ግን ይኸው ደሞዝ የሚከፍላቸውን ህዝብ ነው::
ህገ መንግስት አዋጅ መመሪያ አያለ መንግስት የሚያወጣው እና ፓርላማ አጸደኩ የሚለው ለህዝቡ ምንም የሰጠው ትርጉም የለም ጠቀሜታውም ዜሮ ነው ህዝቡ በኑሮ ውድነት እየደቀቀ ባለበት ሰአት ላይ ጥቂት ሰዎች ገነው በኢኮኖሚ መበልጸጋቸው በማህበራዊው መስክ የሚደረገውን ህብረተሰባዊ ጠቀሜታዎችን ማሳጣታቸው የፍትህን በአደባባይ መሰቀል ያመለክታል:: ይህ ሁሉ ተያይዞ የጸጥታ ሃይሎች ህዝብን አይዞህ ባይነታቸውን ትተው የባለስልጣናትን ወንበር እየጠበቁ ነው:: ስለዚህ ለመንግስት አስፈላጊውን ግብር እና ቀረጥ እስከከፈልን ድረስ የጸጥታ አስከባሪዎች ስራ እና የህገመንግስቱ ትርጉም ይነገረን::ፍትህ ላይ እናተኩር::