የቀድሞ የብኣዴን እና የኦሕዴድ ታጋዮች የነበሩ የሰራዊቱ የጦር መኮንኖችን ለመቀነስ ታቅዷል:: የአሸባሪነት ሕጉን በሕገመንግስቱ ውስጥ በስልት ለማካተት ጥናት ሊጀመር ነው::

የአንድ ብሄር የበላይነት እና አድሏዊነት ካልተወገደ ሰራዊቱ እንዳይታመስ ያሰጋል::

በወያኔ እና በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት የጦር መኮንኖች እና ወታደሮች መሃል ጋብ ያለው ጡዘት ጊዜውን እየጠበቀ እየገነፈለ መሆኑን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ለምንሊክ ሳልሳዊ በላኩት መልእክት ጠቁመዋል::በሕወሓት ጄኔራሎች የሚመራው የመከላከያ ሰራዊቱ የበታች የጦር መኮንኖችን ከዚህ ቀደም ለመከላከያ ደህንነት ቢሮ ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት ከሰራዊቱ መቀነስ ያለባቸው የቀድሞ የብኣዴን እና የኦሕዴድ ታጋዮች የነበሩ የጦር መኮንኖች ዝርዝር ተጠንቶ ለኢታማጆር ሹሙ የቀረበ እና ይህንንም መሰረት አድርጎ መኮንኖቹን ከሰራዊቱ ውስጥ ለመቀነስ መታቀዱን ምንጮቹ ገልጸዋል::

እንደ ምንጮቹ መረጃ ከሆነ ከቀረቡት 2369 ከምክትል መቶ አለቅነት እስከ ኮሎኔልነት ማእረግ ያላቸው የቀድሞ የበረሃ ታጋዮች የአሁን መኮንኖች ውስጥ አላስፈላጊ የሚባሉት ተጣርተው ከሰራዊቱ በዳረጎት የሚቀነሱ ሲሆን ከደርግ ስርኣት ጋር ቁርኝት የነበራቸው ከብሄራዊ ውትድርና ሰራዊቱን የተቀላቀሉት በቦርድ እና በጤንነት እክል በጡረታ የሚሰናበቱ እንዲሁም በማስጠንቀቂያና በደምወዝ ቅጣት የሚታለፉ እንዳሉም ታውቋል:: ይህንን ሁሉ ችግር የፈጠረው በመሃከላቸው የተነሳው የአንድ ብሄር የበላይነት እና አድሏዊነት የዘር ቆጠራ የፖለቲካ ሕዝባዊ ጥያቄዎች እና የሕገመንግስት ተግባራዊነት ክርክር የጫረው አለመግባባት ሲሆን በሰርኣቱ ውስጥ የተጠየቀው የጥቅማ ጥቅም ጥያቄም ሌላኛው መነካከሻ መሆኑን ምንጮቹ ተናግረዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሃገር ውስጥ እና በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቃውሞ እየደረሰበት ያለውን የወያኔውን የአሸባሪነት ሕግ በሕገመንግስቱ ውስጥ ለማካተት ጥናት ሊጀመር ሲሆን ከዚህ ቀደም እንደነበረው የአደገኛ ቦዘኔዎች ሕግ በሂደት አይን እያየ አሁን ያለውን የአሸባሪነት ህግ ማክሰም የሚል ሃሳብ ተይዞ ጥናቱ እንደሚካሄድ ታውቋል::ምንልክ ሳልሳዊ