‹‹ፖለቲካ›ንማ ፊት ለፊት ነው
……………..
ጌታቸው ሽፈራው በእኛ አገር በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ‹‹ፖለቲካ›› የሚባለው መብት መጠየቅ፣ እውነታውን መጻፍና መናገር ነው፡፡ ስለ ውሃ እጥረት፣ ሙስና፣ መብራት፣……ጮኽ ብሎ ያወራ ከዘመድና ጓደኛው ‹‹ይህን ፖለቲካህን ተወን!›› ይባላል፡፡ ፌስ ቡክን ጨምሮ በአብዛኛዎቹ ሚዲያዎች ደግሞ እነዚህን መሰረታዊ መብትና አቅርቦቶች ላይ የሚነሳውን ፖለቲካ ለማለዘብ (ለመራቅ) ‹‹ፖለቲካን በፈገግታ፣ የፖለቲካ ቀልዶች፣ የፖለቲካ ሽሙጥ፣……ፖለቲካን በጎሪጥ…..›› የሚባሉ አቀራረቦች ተለምደዋል፡፡
በተቃራኒው ገዥዎች ህዝብን የሚበድሉት፣ የሚዘርፉት፣ የሚያሰቃዩት ፊት ለፊት፤ በገሃድ ነው፡፡ ስለ መብት የሰበኩ ፖለቲከኞች፣ ስለ ለውጥ የጻፉ ጋዜጠኞች፣ ስለ እምነታቸው ያስተማሩ አማኞች ‹‹ሽብርተኛ›› ተብለው ታስረዋል፡፡ በርካታ ህጻናትና እናቶች ጎዳና ላይ ጸሃይና ቁር እየተፈራረቀባቸው እየተመለከትን ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ተከልክሏል፡፡ ሚዲያዎች በተራ ካድሬ ትዕዛዝ ይዘጋሉ፡፡ በዚህ ዘመን አገር እየተሸጠ ነው፡፡ ስሙን በቅጡ የማይጽፍ ‹‹ታጋይ››ና ካድሬ የማይገባውን ደም ወዝ ሲከፈለው ባለ ዲግሪዎቹ አንድ ቀን ያልተማሩትን ድንጋይ ፈለጣ በአማራጭነት ቀርቦላቸዋል፡፡ ለኢትዮጵያውያን የተነፈገው ለም መሬት ለሳውዲና ለህንዶች በሲጋራ ዋጋ እየተቸበቸበ ነው፡፡ ….ኧረ ስንቱ!?
ይህ እንግዲህ ፊት ለፊት የምናየው መራራ ሀቅ ነው፡፡ ታዲያ ለዚህ አይን ያፈጠጠ ጭቆና፣ በደል፣ አምባገነንነት የምን ፈገግታ ነው? ምንስ ይቀለድበታል? እንዴትስ በጎሪጥ ይታለፋል? በእርግጥ ህዝባችን ‹‹ፖለቲካ›› ብሎ በጠባቡ የሚተረጉመውም ይሁን ከዚህ የሚሰፋው ፈገግታ፣ ቀልድ፣ ድርድር፣ ስምምነት፣ መመቻመች……አያስፈልገውም እያልኩ አይደለም፡፡ በእኛ አገር ደግሞም በአሁኑ ወቅት ግን ፖለቲካው ፊት ለፊታችን የተደቀነ፣ የእያንዳንዱን ቤት ያንኴኳ፣ አገር ያከሰረ፣ ህዝብን ያዋረደና ያስናቀ ሆኗል፡፡ ይህን ፖለቲካ በፈገግታ፣ በሹክሹክታ፣ በለበጣ፣ በጎሪጥ፣ በአሽሙር እንለፈው ካልን አሽሙሩም፣ ቀልዳ ቀልዱም፣ ለበጣውም በራሳችን ላይ መሆኑ ነው፡፡ መርጉ የተጫነን እኛውን ራሳችን ላይ ነውና!
ከወራት በፊት ነው፡፡ ውሃ ለመቅዳት ተሰልፈን ከተሰለፉት ጋር ለአቅርቦቱ ችግር የ‹‹መንግስት››ን ድክመት አንስተን እንወያያለን፡፡ ‹‹ቀለል›› ባሉ ጉዳዮች አብሮን ሲያወራ የነበረ ወጣት ‹‹አይ እኔ ፖለቲካ አልወድም! አታነካኩኝ!›› ብሎን ራሱን ‹‹ነጻ አወጣ!››፡፡ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ይቺ ሽሽት የተለመደች ስለሆነች አልገረመኝም፡፡ አንድም ወሬውን የሚያስጀምረው ሰው ጆሮ ጠቢ ይሆናል፣ አሊያም ለጆሮ ጠቢ ያጋልጠኛል ከሚል ፍርሃት የመነጨ ሳይሆን አልቀረም፡፡ ጥቂት ከቆየን በኋላ ወጣቱን ስለራሱ ስጠይቀው በሹክሹክታ ስለዚህ መንግስት ብልሹነት ማውራት ጀመረ፡፡ አባቱ የደርግ ወታደር ከተባለው የአገሪቱ ሰራዊት በግፍ ተባረዋል፣ 97 ላይ አባቱ ታስረው ስቃይ ደርሶባቸዋል፣ አባል ባለመሆኑ ለአንድ አመት ተኩል ስራ አላገኘም፣ በግድ የድጋፍ ሰልፍ ይወጣሉ፣ ቤታቸው ውስጥ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው……….፡፡
ይህ ፖለቲካው መርግ የሆነበት፣ በብልሹ ፖለቲካው እስከ ምናምኑ የተነከረ ልጅ ነው እንግዲህ ‹‹አታነካኩኝ!›› የሚለው፡፡ ከዚህ ውጭ ምን ሊያደርጉት እንደሚፈልግ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ፌስ ቡክም ሆነ ሌላ ቦታም ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞኛል፡፡ በደል የደረሰበት ሰው ዜና ልትዘግቡለት ስትሉ ‹‹አይ ያጠብቁብኛል፣ ትንሽ ቆይ!፣ ለስለስ አድርገው፣ እንዳታስመታኝ፣….›› ይላችኋል፡፡ ገዥዎቹ ደግሞ ይህን ይወዱታል፡፡ የሹክሹክታ፣ የለበጣ፣ የሀሜት፣ የፈገግታ……‹‹ፖለቲካ›› ከልኩ እንደማያልፍ ያውቁታል፡፡ እነሱ ፊት ለፊት እየበደሉ፣ የጎሪጥ እያየ የሚያልፍ፣ በቅኔና ቀልድ የሚናገር ህዝብ ለስልጣናቸው በእጅጉ ምቹ ሆኖላቸዋል፡፡
እኔም እላለሁ! መብታችን ለማስከበር፣ አቅርቦት ለማግኘት፣ ክብራችን ለማስጠበቅ፣……..መናገር፣ መጠየቅ፣ መቃወም ያለብን እንደወረደ፣ ፊት ለፊት እንጅ ቀልድ፣ ፌዝ፣ ቅኔ፣ አሽሙር፣ ሽሙጥ የሚያስፈልገን ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡