“ግድብ ሲጠናቀቅ የግብፅ ፖለቲከኞችን ዓይን ይከፍታል::ግብፃውያን ዛቻን ትተው ገንቢ በሆኑ ስራዎች ማተኮር አለባቸው::” ውጭ ጉዳይ

"ግድብ ሲጠናቀቅ የግብፅ ፖለቲከኞችን ዓይን ይከፍታል::" አምባሳደር ዲና
"ግብፃውያን ዛቻን ትተው ገንቢ በሆኑ ስራዎች ማተኮር አለባቸው::" ውጭ ጉዳይ

በማንኛውም አገር ወንዙን በብቸኝነት ለመጠቀም የሚነሳ ፍላጎትና ታሪካዊ መብት ለማስቀጠል የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም። ግብፃውያን ፋይዳ የሌለው ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚ ማዕቀብና ዲፕሎማሲያዊ ዛቻዎችን ትተው ገንቢ በሆኑ ስራዎች ማተኮር እንደሚገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምበሳደር ዲና ሙፍቲ ለኢዜአ እንደገለፁት የተለያዩ የግብፅ ባለስልጣናት፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ፖለቲከኞች በየጊዜው የሚለቋቸው ዛቻዎች ተገቢ አይደሉም ፋይዳም የላቸውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ዛቻን በዛቻ አይመልስም ያሉት ቃለ አቀባዩ ዛቻ በየትኛውም ነገር ጥቅም እንደሌለው ገልፀዋል።እንደ አምባሳደር ዲና ገለፃ ለግብፅም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅመው ተባብሮ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ከሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በጋራ በመስራት ተጠቃሚ ሲሆኑ ብቻ ነው።የናይል ወንዝ የአንድ አገር ስጦታ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ስጦታና ሁሉም እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት የጋራ ወንዝ መሆኑንም አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል።

አምባሳደር ዲና እንደተናገሩት በማንኛውም አገር ወንዙን በብቸኝነት ለመጠቀም የሚነሳ ፍላጎትና ታሪካዊ መብት ለማስቀጠል የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም።ግብፃውያን የናይል ጉዳይ በህገ መንግስታቸው መስፈሩ ሳይሆን ጠቃሚው ከተፋሰሱ አገራት ጋር ፍትሃዊና ማንንም የተፋሰሱ ሀገር በማይጎዳ መንገድ የናይል ወንዝን ለመጠቀም የተፈረመው የኢንተቤ ስምምነት መቀበል መሆኑን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

አምባሳደር ዲና የኢንቴቤ ስምምነትን አለመቀበል ከሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ጋር ያቀያይማልም ብለዋል። አንድ አገር ህግ ሲያወጣ በማንኛውም ነገር የሌላ አገር ጥቅም የሚጎዳ መሆን የለበትም ያሉት ቃለ አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተፋሰሱ አገሮች የሚወጡ የውሃ ህጎች ከዓለም ዓቀፍ ውሃ ህጎች ጋር የሚጋጩ መሆን የለባቸውም፡፡ የዓለም ዓቀፍ ህጎችም አይፈቅዱም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር ዲና እንዳሉት በካርቱም በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል ሲካሄድ በነበረው ውይይት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ስብሰባዎች የዓለም ዓቀፍ ኤክስፐርቶች ፓናል አጥንቶ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ ተግባራዊ የሚያደርግ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማምተው ነበር፡፡ ነገር ግን ግብፆች በሦስተኛው ስብሰባ ባመጡት አዲስ ሃሳብ ምክንያት ውይይቱ ያለ ቀነ ቀጠሮ መበተኑን አስታውሰዋል፡፡ ውይይቱ ያለ ቀነ ቀጠሮ የተበተነበትም ምክንያት በግብፅ በኩል ዳግም ጥናት የሚያካሂድ የውጭ ዜጎችን ያካተተ አዲስ ዓለም ዓቀፍ ኮሚቴ የመመስረትና ያጠናው ውሳኔ ተግባራዊ ይሆናል በሚል የቀረበው ሃሳብ በኢትዮጵያና ሱዳን በኩል ውድቅ በመደረጉ እንደሆነ የገለፁት አምባሳደር ዲና ውይይቱ ወደ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ማዘንበሉም ሌላው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ግብፃውያን ጠቃሚው ገንቢ አቋም መያዝ ነው ብለው ጥርጣሬን ትተው የዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች ፓናል አጥንቶ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ ደጋግመው ሊያዩት እንደሚገባ ጠቁመዋል።አምባሳደር ዲና ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የተፋሰሱን አገሮች ጥቅም አይጎዳም ይበልጥ የተፋሰሱ አገራት በኢኮኖሚ የሚያስተሳስር መሆኑን ገልፀው ግድቡ በመላው ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ቀን ከሌት እየተሰራ መሆኑንና ለአፍታም እንኳን ሳይቋረጥ ያለ ምንም የውጭ ዕርዳታ ግንባታው እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ጥሩ ግንኙነት ይፈጠራል፤ ይህም የተሳሳቱ የግብፅ ፖለቲከኞችን ዓይን ይከፍታል ብለን እናስባለን ብለዋል።