ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የሚወድቁት ስህተት ስለሚሰሩ ሳይሆን ስህተታቸውን እንዴት እንደሚያርሙ ስለማያውቁ ነው፡፡ ወደኃያላን መንግሥታት ስናንጋጥጥ የራሳችንን ህዝብ እንረሳለን፡፡
ምንሊክ ሳልሳዊ:-በጭካኔ ፍትሕን ማምጣት እና የኢኮኖሚ አምባገነንነት ቦታ ቦታ አላቸው፡፡ ጊዜ ጊዜም አላቸው፡፡ ለመተግበር ፍፁም ጥንቃቄን ይጠይቃሉ። ውጤታቸው ጠላት ማብዛት፣ ዜጋን ማስኮረፍ፣ ሕዝብን መሬት ውስጥ መክተት ሊሆን ይችላል፡፡ ሆደ – ሠፊና ለጋሥ አምባገነን መሆን የዋዛ ነገር አይደለም፡፡ ህብረተሰብን በቅጡ ማሳመን ይሻል፡፡ በተለይም የተለያየ ሃይማኖት፣ ባህልና ብሔረሰብ ባለበት አገር እጅግ ከባድ አስተዳደራዊ ምሉዕነትን ይጠይቃል፡፡
ኃያላን መንግሥታት ሲሻቸው የበኩር ልጅ፣ ሲሻቸው የእንጀራ ልጅ ማድረግን ይችሉበታል፡፡ ኃያላን መንግሥታት “ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ” ገንፎ መብላትን ያውቁበታል፡፡ መልዕክተኞቻቸውን ሲሻቸው በእርዳታ ሰጪ መልክ፣ ሲሻቸው በሚሲዮናውያንና በሃይማኖተኞች መልክ፣ ሲሻቸው በዲፕሎማት መልክ፤ ካልሆነም በቀጥታ ስለላ መልክተኞች – አሊያም በቱሪስት ወይም በፒስኮር መልክ ይልካሉ፡፡ ከከፋም የውስጥ ዐርበኛ ይቀጥራሉ፡፡ ላላ ያለ ካገኙም አገራቸው ድረስ ጋብዘው፣ አስተናግደው ሾመው፣ ሸልመው አንቱ ብለው ይቀባሉ፡፡ያለ፣ የነበረ ወደፊትም የሚኖር ዘዴያቸው ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ካልተሳካ የቁርጡ ቀን መጣ ማለት ነውና እንደ ኢራቅ የጦር ዘመቻ ያካሂዳሉ፡፡ እንደግሎባላይዜሽን አበጋዞች ሳይሆን እንደጥንቶቹ ቅኝ ገዢዎች- በግልጽ ወረራ ያካሂዳሉ፡፡
ከሁሉም ይሰውረን፡፡ ሲያወድሱ ሰማይ፣ ሲጥሉ እንጦር አውርደው ከትቢያ ይደባልቃሉ፡፡ የሁልጊዜ መሳሪያቸው ነው፡፡ እስካመቸናቸው እስካልቆረቆርናቸው ድረስ ያለእኛ በትክክለኛው የዕድገት መስመር ላይ ያለ አገር አይገኝም፡፡ “እንዲህ እያልሽ ውቴልሺን ሽጪ” እንዳለው ወሎ፤ የሚነግራቸው ጠፍቶ ነው፡፡ ለእነሱ የከፋን ለታ ግን ያለእኛ ኋላቀር፣ ያለእኛ ደንቆሮ፣ ያለእኛ ጦርነት ናፋቂ፣ ያለእኛ ረሃብተኛ፣ ያለእኛ መናጢ ደሃ የለም፡፡ ”እፀድቅ ብዬ ባዝላት ተንጠልጥላ ቀረች” ይሉናል፡፡
ከበረታን፤ “አላህንም አትክዳ፣ ሐረጓንም አትልቀቅ” እንዳሉት ጠቢብ ማሰብ አለብን፡፡
የኃያላኑን የቢዝነስ ኮሙኒቲ አይተን እኛ ምን እንሥራ ማለታችን ደግ ነገር ሆኖ፤ ከእዚህ ሁሉ በስተጀርባ ምን አለ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ ምን ያህል ከልባቸው ነው? እነሱ፤ ለህዝባችን ይበጃል ያሉትን ማንኛውንም እኩይ ተግባር ከመፀፈም ወደኋላ ብለው ያውቃሉን? ብለን እንጠይቅ፡፡ ሁሉንም በትጋት በጉጉት – ዐይን እናስተውል፡፡
የፖለቲካ ፀሐፍት እንደሚነግሩን፤ “ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የሚወድቁት ስህተት ስለሚሰሩ ሳይሆን ስህተታቸውን እንዴት እንደሚያርሙ ስለማያውቁ ነው፡፡ ይሄ የእኛም ችግር ነው፡፡ ሁለት ተጠቃሽ ባህሪዎቻችን፡- “ካፈርኩ አይመልሰኝ ፣ እና “የአብዬን እከክ ወደእምዬ ልክክ ናቸው፡፡ የሠራሁት ነገር ስህተት እንዳለበት ቢነገረኝም አልለቀውም፡፡ አንዴ አድርጌያለሁ ብያለሁ፡፡ ብያለሁ፡፡ ኃያላኑም ተናግረዋል፤ ማለት አይበጅም፡፡ በተቻለ መጠን በኃያላን ውዳሴ አለመማለል ብልህነት ነው! “ቅጥ – ያጣ መረጃ” ይዘን ነው እስካሁን የሄድነው ተብሏል፡፡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮቻችን፣ የሚጨበጡትንና የማይጨበጡትን ጨምሮ፤ ስፍር – ቁጥር የላቸውም፡፡ በአንድ የድህነት ባኮ ከትተን ልንገላገላቸው መንገድ ከጀመርን ከራርመናል፡፡ አሁንም ግን በመጨለምና በንጨላጨል መካከል ነን፡፡
በሬዲዮ ጥያቄና መልስ ፕሮግራም “የሱዳን ዋና ከተማ ማን ትባላለች” ሲባል “አማርኛ ይሁንልኝ” …“የቆጡን አወርድ ብላ…” ጨርሰው ሲባል “ስፖርት ይሁንልኝ”፤ ዓይነት መልስ የሚመልስ ህብረተሰብ ይዘን እየዳከርን ነው፡፡ አገራችን፤ ላዩም ታቹም ይሄን መሳይ ነው!ሰማይ ሰማይ ስናይ እግራችን ሥር ያለውን ነገር አንዘንጋ፡፡ ሰማዩን አተኩረን ስናይ ቀልባችን ሙሉ በሙሉ እሱ ላይ ብቻ ካረፈ፤ ከሥር እግራችንን የሚመታንን እንቅፋትና የሚያሰምጠንን ጉድጓድ አናየውም፡፡ ወደኃያላን መንግሥታት ስናንጋጥጥ የራሳችንን ህዝብ እንረሳለን፡፡ አልፈን ተርፈንም የሰዎችን ዕጣ-ፈንታ ስንናገር የራሳችንን ዕጣ-ፈንታ ሳናቅ እንዳንቀር እንጠንቀቅ!