የተከበራችሁ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሆይ! በጠንካራ ወኔ ዛሬም ጥሪያችንን እናስተጋባለን!! ድምጻችን ይሰማ!

60ኛው የ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› በራሪ ወረቀት አቢይ ጽሁፍ እነሆ!
በጠንካራ ወኔ ዛሬም ጥሪያችንን እናስተጋባለን!!

የተከበራችሁ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሆይ! ‹‹ሀይማኖታዊ መብታችን ይከበር!›› ስንል የምናደርገው ሰላማዊና ህዝባዊ ትግል ዛሬ ወሳኝ ምእራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ይኸውም የምንገኝበት የእፎይታ ጊዜ ሊነሳ አጭር ግዜ በቀረበት በዚህ ሰዓት ሰላማዊ ትግሉ የተጀመረበት ሁለተኛ ዓመት የሚታወስበት ወቅት ላይ መድረሳችን ነው፡፡ ከፊታችን ጁሙዓ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት ሁለተኛ ዓመት የሞላውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ የ‹‹መብቴ ይከበርልኝ!›› ጥያቄ በተለያዩ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች መዘከር እንጀምራለን፡፡ በዚህ ሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በዝምታችን ውስጥ አልፈው የሚያስተጋቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን እናደርጋለን፡፡ የእፎይታ ጊዜው ዝምታ አንዱ የሰላማዊ እንቅስቃሴያችን መገለጫ ሆኖ ላለፉት 6 ወራት ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ የእፎይታ ጊዜው የመጨረሻ እድሜ ላይ የምናደርገው የሁለት አመቱን የሰላማዊ ጥያቄያችንን ሂደት የምናስታውስበት እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም የሁለት አመት ጉዟችንን በምናስታውስበት ሂደት ሁሉም የሙስሊም ማህበረሰብ ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርግ ‹‹ድምፃችን ይሰማ!›› ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ሰላማዊ እንቅስቃሴያችን ሰላማዊ ሆኖ በመጓዝ ሰላማዊነቱን ለማደፍረስ መንግስትና ህገ ወጡ መጅሊስ የሚሰነዝሩትን የስም ማጥፋት ዘመቻ፣ የሚያሴሩትን ሴራ ወጥመድና እና ህገ መንግስቱን ክፉኛ የሚሸረሽሩ ህገ ወጥ ተግባራት ሁሉ በአላህ ፈቃድ እያከሸፈ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ኢንሻላህ ወደፊትም በሀያሉ ጌታችን አላህ ፈቃድ የእምነት ነፃነታችን ተከብሮ በሀገራችን ፍትህን እንደምንጎናፀፍ እምነታችን ሙሉዕ ነው፡፡ ይህን የምንለው ሀያሉ ጌታችን አላህ የተበደለን የሚክስ፣ በህዝብ ላይ ግፍ የሚፈፅምን መሪ የሚያስተካክል አልያም የሚቀይር ሁሉን ቻይና ተመልካች በመሆኑ ነው፡፡ ጌታችን አላህ በተከበረው ቃሉ እንዲህ ይለናል ‹‹…… ምእመኖቹንም መርዳት በእኛ ላይ ተገቢ ሆነ፡፡›› (ቅዱስ ቁርዓን 30፡47)

ዛሬ ላይም ቆመን ለሚመለከተው ሁሉ የምናረጋግጠው እውነታ ትግላችን ከስሜታዊነት ርቆ በሀቅ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው፡፡ ትግላችን ‹‹የሀይማኖት ነፃነታችን ይከበር! በገዛ ሀገራችን በሀይማኖታችን የሚፈፀምብን ግፍ ይቁም!›› ነው፡፡ ትግላችን ‹‹ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ የሚገኙ እስር ቤቶች የህግ ታራሚዎች የሚቆዩበት ስፍራ መሆናቸው ቀርቶ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ማሰቃያና ማጎሪያ ስፍራዎች እስኪመስሉ ድረስ እየተደረገብን ያለው ዓይን ያወጣ የመብት ረገጣና የህገ መንግስት ጥሰት ይቁም!›› ነው፡፡ ‹‹የህዝብን መብት እንዳሻቸው ረግጠውና የሀይማኖት ነፃነትን ነፍገው ሲያበቁ ይህን ፍፁም ህገ ወጥና ክፉ ስራቸውን ለመሸፈን በማሰብ በተቃራኒው በሚዲያ ቀርበው በየእለቱ ‹አክራሪ፣ አሸባሪ፣ ፅንፈኛ፣ ህገ መንግስቱንና የሌሎችን እምነት መኖር የማይቀበሉ› ሲሉ የሚያቀርቡት የተገላቢጦሽ ልፈፋና ድራማ ህዝብ አንቅሮ የተፋው እዚህ ግባ የማይባል ከንቱ ድካም መሆኑን ደግመው ይገንዘቡ›› ነው፡፡ ‹‹ለልማት መዋል የሚገባው የሀገር ሀብት እና ጊዜ የንፁሁን ህዝበ ሙስሊም ስም ለማጥፋት፣ የህዝበ ሙስሊሙን ሀይማኖታዊ ነፃነት እና ህገ መንግስታዊ መብትን ለመገደብ፣ ህዝብ በይፋ ያወረዳቸውን የመጅሊስ ሹመኞች ከህዝበ ሙስሊሙ ተቃራኒ ተሰልፈው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ በማዋል ሀገርን ወደ ፊት ከማራመድ ይልቅ ወደ ኋላ የሚጎትት አካሄድ ላይ መጠመድ ይቁም!›› ነው ጥያቄያችን፡፡ ‹‹እነዚህ ሁሉ ህገ ወጥ ድርጊቶች ቆመውና ጥፋተኞችም በፍትህ ፊት ታርመው የጠየቅናቸው ሰላማዊና ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎች ይመለሱልን!›› እንጂ ሌላ አልነበረም ጥያቄያችን፡፡

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እነኚህን ሁሉ ለግርግር የሚጋብዙ ህገ ወጥ ድርጊቶች እና በደሎችን በእልህ አስጨራሽ ትእግስትና ፅናት ተሻግረው ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህን ያደረግነው ከምንም ነገር በላይ ዲናችን የሚያስተምረንን ሰላማዊነት ለማንፀባረቅ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ እንዲሁም በተመሳሳይ ምንም እንኳ ለሀገር ሰላም እና ለህዝብ ደህንነት መጨነቅ ያለበት አካል በተቃራኒው ተሰልፎ የህዝብን ሰላም እና የተረጋጋ ህይወት፣ እንዲሁም የሀይማኖት እና የግለሰብ ነፃነቶችን በሚያደፈርሱ ተግባሮች ላይ ሲጠመድ ብናስተውልም ነገር ግን እንደ ህዝብ ለሀገራችን እና ለህዝቦቿ መረጋጋት በማሰብ፣ ለሰላሟ እና ደህንነቷ በመጨነቅ፣ በሰከነ ልቦናና በተገራ የሀላፊነት ስሜት እልህ የሚያስጨርሱ ክስተቶችን በሚያስደንቅ ፅናት፣ አንድነት እና ትእግስት አልፈናል፡፡ ይህ እንደ ህዝብ በአላህ እገዛ የተቸርነው ፀጋ ነውና አልሐምዱሊላህ!!

የእፎይታ ጊዜውም ቢሆን የተቀመጠበት ዋነኛ ዓላማ ይህንኑ ከግንዛቤ በማስገባት መንግስት ከስሜታዊነት ወጥቶ በሰከነ መንፈስ ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄ እንዲያስቀምጥ የማሰቢያ እና የማሰላሰያ ጊዜ መስጠት ነበር፡፡ በተመሳሳይ ‹‹ተቃውሞ ቢቆምና ሙስሊሙ ዝም ቢል መንግስት ምን ሊያደርግ እንደሚችል በተግባር በማየት ማረጋገጥ›› የሚሉና መሰል ዓላማዎችም ነበሩት፡፡ በመሆኑም መንግስት በዚህ የእፎይታ ጊዜ ከፈፀመው ስህተት ከመመለስ ይልቅ በዚያው የስህተት መስመር መጓዙን እንደቀጠለ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ተቃውሞ የሌለበት አየር ቢመጣም እንኳ እስሩ፣ ድብደባው፣ እንግልቱ፣ የኢማሞች መባረርና መንግስታዊ ኢማሞች መተካቱ፣ የመስጂድ ነጠቃው፣ የሀሰት ክሱና የሀሰት ፍርዱ ሁሉ እንደሚቀጥሉ እንጂ እንደሚቆሙ የእፎይታ ጊዜው አላሳየንም፡፡

በመሆኑም በዚህ የእፎይታ ጊዜው የመጨረሻ እድሜ ላይ የትግላችንን የሁለት ዓመት ጉዞ ስናስብ በሙሉ መነቃቃት ላይ በመሆን ነው፡፡ በጠንካራ ወኔ ዛሬም ጥሪያችንን እናስተጋባለን፡፡ ዛሬም እንደ ትላንቱ ሁሉ ለዲናችን መከበር ዘብ በመቆም ሀይማኖታዊ ነፃነታችንን እስክንጎናፀፍ እና የፈጣሪያችንን አምልኮተ ህግጋቶች እንዳንተገብር፣ ብሎም እንድንርቅ በማሰብ የሚደረጉብን ጫናዎች እስኪቆሙ ድረስ ሰላማዊ ሆነን ከመታገል አንወገድም፡፡ ዛሬም አንድነታችን እንደጠበቅን ለዲናችን መከበር ያለንን ጠንካራ ወኔ አጉልተን እናሳያለን፡፡ ሂደታችን ሰላማዊና ከግብታዊነት የራቀ፣ ሀይማኖታዊ መብት እንዲከበር የመጠየቅ ሂደት ነውና የጠየቅነው መብት እስኪከበር በተለያዩ ሰላማዊ መንገዶች መታገላችንን እንቀጥላለን፡፡

የምንከፍለው መስዋእትነት ለዲናችን መሆኑን ጠንቅቀን መረዳታችን በሰላማዊ ትግሉ ላይ አላህ ወፍቆን በምንከፍለው መስዋእትነት ሳቢያ የምናገኘውን ደረጃ ማሰብ ምንኛ የሚያጓጓ ፀጋ መሆኑን ግፍ የሚፈፅሙብን አካላት በጥልቀት እንዲረዱት ደግመን የምናስመሰክርበት ሂደት ላይ ነን፡፡ ውድ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች! ከኛ የሚጠበቀው ዲንን በመጠበቁ ሂደት ላይ ሁሉም በሚችለው አቅም መረባረብ ነው፡፡ ይህን ስናደርግ ውስጣችን በሚከተለው የሀያሉ ጌታችን አላህ ቃልኪዳን ይረጋጋል፡-

‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን (ሀይማኖቱን) ብትረዱ ይረዳችኋል…›› (ቅዱስ ቁርዓን 47፡7)

አዎን! እስልምናችንን ለመጠበቅ በምናደርገው እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ያለጥርጥር የአላህ አርዳታ ከጎናችን ይሆናል፤ በንፁህ ልቦና በአላህ መንገድ ላይ እስከቆምን ድረስ፡፡ አላህ ባዘዘው መንገድ ላይ መቆም ምንኛ መታደል ነው!!

በሌላ መልኩ ለዲናችን የምንከፍለው እያንዳንዱ መስዋእትነት ዋጋው አላህ ዘንድ እንጂ የትም አይደለም፡፡ ሺዎች ታስረናል፤ አልያም የግፍ በትር አርፎብናል፡፡ ከእስር የተረፉ ብዙ አሊሞቻችን፣ ዱዓቶቻችን እና ወጣቶቻችን ተሰደዋል፤ ተወልደው ካደጉባት፣ ኖረው ከከበዱባት የገዛ ሀገራቸው ሰላምን ፍለጋ እንዲሰደዱ ተገደዋል፡፡ ወጣት አዛውንት፣ ወንድ ሴት ሳይለይ የከፈልናት እያንዳንዷ መስዋእትነት ጌታችን ዘንድ ተመዝግባ ለምንዳ ትቀመጣለች፡፡ አዎን! ዛሬን ስለ ዲኑ እና ህብረተሰቡ በመቆርቆር፣ ሀቅን በመናገር፣ ሙስሊሞችን ወደ አንድነት በመጣራት ጊዜውን ያሳለፈ ወጣት ነገ ጌታው ዘንድ ትልቅ ክብርን ይጎናፀፋል፡፡ ጌታችን አላህ በተከበረው ቃሉ እንዲህ ይላል፡-

‹‹… እነዚያም የተሰደዱ፣ ከአገሮቻቸውም የተባረሩ፣ በመንገድም የተጠቁ (በአላህ መንገድ ላይ ግፍ የተፈፀመባቸው)… ክፉ ስራዎቻቸውን በእርግጥ አብሳለሁ፤ በስሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በእርግጥ አስገባቸዋለሁ፤ ከአላህ ዘንድ የሆነን ምንዳ (ይመነዳሉ)፤ አላህም እርሱ ዘንድ መልካም ምንዳ አለ፡፡›› (ቅዱስ ቁርዓን 3፡195)

ዛሬም አንድነታችንን እንደጠበቅን ለዲናችን መከበር ያለንን ጠንካራ ወኔ አጉልተን እናሳያለን!! የፈጣሪያችንን አምልኮተ ህግጋቶች እንዳንተገብር ብሎም እንድንርቅ በማሰብ የሚደረጉብን ጫናዎች እስኪቆሙ ድረስ ሰላማዊ ሆነን ከመታገል አንወገድም!! ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!

ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!