ኢትዮጵያ :- ተቃዋሚ ፖለቲከኝነት የትርፍ ሰአት ስራ እና የፖለቲካ ኪሳራ

ምንሊክ ሳልሳዊ:-የትርፍ ሰአት ፖለቲካ በህዝብ ላይ የሚሴር ያልታወቀ እና ያልተነቃበት ሴራ ነው::ይህ ማለት ፖለቲከኞቹ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ በሃሊዮ ወላ በገቢር የህዝብን የመኖር ደህንነት አደፍርሰዋል ::ራሳቸውንም ኢእውቀታዊ ወደሆነ የፖለቲካ ኪሳራ አዘቅት ልከውታል:: ታዲያ ለእነዚህ የትርፍ ሰኣት ፖለቲከኞች ወይም ሴረኞች እንበላቸው ጸረ ህዝብ እና ጸረ ሰላም የሚል ታርጋ ይነሳቸው = ወያኔን አሸባሪ ማፊያ አድፍጦ ገዳይ አፋኝ ወዘተ ስንለው እነዚህን ታቃዋሚ እና ታማኝ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ሂደታቸው ላይ ያልነቁ ደበኞች ብንላቸው ሲያንሳቸው ነው::

ተቃዋሚ ፖለቲከኝነት በብዛት የትርፍ ሰአት ስራ የሆነባት ኢትዮጵያ አንድም ከወያኔ ቅጥረኝነት ሌላም ከፖለቲካ ከሚገኘው ጥቅም የተትረፈረፈ የህይወት ስኬት ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ አስመስሎታል::ያለፉት 22 አመታት መለስ ብለን ስናስበው የሽግግር ወቅት እንዲመሰረት ወያኔ ከፈጠራቸው የአናሳ ድርጅቶች እና በኋላም በተቃዋሚ ስም እንዲንቀሳቀሱ ተደርገው የምክር ቤት ወንበር እስከመያዝ የደረሱት ፖለቲከኞች አንድም የዩንቨርስቲ መምህር ናቸው አሊያም የግል ስራቸውን የሚያሯሩጡ እና በትርፍ ሰኣታቸው ገንዘብ ላለማጥፋት ወደ ፖለቲካው ያዘነበሉ አሊያም ከገዢው ፓርቲ ዳጎስ ያለ ጉርሻ አግኝተው የሚኖሩ ግለሰቦች ናቸው::

የትርፍ ሰአት ፖለቲካ የሚመነጨው ከግለኝነት ስለሆነ በሃገር ላይ የሚደረጉ ህዝባዊ አብዮቶችን እና ለውጦችን በምናገባኝነት ስሜት(አስመሳይነት) እንዲመለከቱት ያደርጋል;ፕሮፓጋንዳን ብቻ ለፖልቲካ ፍጆታነት የመጠቀም ስልት ማለትም ነው::ግለኝነት ስንል ፖለቲከኛው በፖለቲካው ረገድ መጫወት ያለበትን ሚና ረስቶ ከፖለቲካው ከሚገኘው ጥቅም ላይ ስለሚያተኩር ሲሆን ህዝባዊነትን ገደል ይከተዋል:: ወያኔዎች እያንዳንዳቸው ፖለቲካውን ስራዬ ብለው ስለያዙት በፖለቲካው መስክ ያላቸው ስኬት በዲሞክራሲ ስም ወደ አምባገነንነት አድጓል::

የትርፍ ስራ ፖለቲካ ሌላ ያዋጣቸው ለታማኝ ተቃዋሚዎች ነው::ታማኝ ተቃዋሚዎች ከተቃሚነት ሌላ የፖለቲካ ስለላ ያካሂዳሉ:: የፈለጉትን የትምህርት ዘርፍ ይማራሉ::አስፈላጊው የውስጥ እና የቅርብ ርቀት ጥበቃ ይደረግላቸዋል::በዚህ ላይ በስልጣን እርከን እንደመምሪያ ሃላፊ የመሳሰሉትን ስልጣኖች ይሰጣቸዋል:: ከዛም ስልጣን ሰበብ ለማስመሰል ይባረራሉ::አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የህዝብ ጥያቄ ሲነሳ ከትርፍ ስራ ተቃዋሚነት ወደ ቋሚ ፖለቲከኝነት በጊዜያዊነት ተመሳስለው ገብተው እንዲያከሽፉት ይደረጋል:: አቤት ታማኝ ተቃዋሚዎች የመንግስትን ወንበር ከያዙት ይልቅ እኮ እነሱ የተመቻቸው ናቸው::

የትርፍ ሰአት ፖለቲካ እያራመዱ ሃገርን እና ህዝብን የፖለቲካ ኪሳራ ላይ የጣሉ የ22 አመታት የፈጠራቸው ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አሁን አሁንማ የኪሳራቸው ውጤት ስድብ ብቻ ሆነ::የትም ላይደርሱ እየተፈራገጡ:: ባለፉት 22 አመታት ጫካ ገብተው ቢሆን እስካሁን የመንግስትን ስልጣን ይዘው ባናፉብን ነበር::በጎረሩብን ነበር:: እኛም ወያኔ ጭራቁን አስወገዱ ብለን ባከበርናቸው ነበር:: እነ ሽማግሌዎቹ ጡረተኛ ፖለቲከኞችም ቢሆኑ በቋሚነት ስላለባቸው ደምብዛት እና ሰኳር ማስታመም ጋዜጣ ማንበብ እና መጻፍ በትርፍ ሰኣታቸው ህዝቡ ትዝ ሲላቸው ተነስተው ይህችኑ ፖለቲካቸውን ይተነፍሱብናል::