ፍትሕ የሚያስፈልጋቸው የሕገወጥ ስደት ሰለባዎች

‹‹ የሌላ አገር ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ በየመንደሩ ገብቶ ዜጎችን ለስደት መለመለ ??? ››
ምንሊክ ሳልሳዊ ብሎግፖስት – በሳዑዲ የዚህ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈውንና ስንቶችን የአካል ጉዳተኛና የአዕምሮ በሽተኛ ያደረገው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ገንዘብ አስተላላፊዎች፣ ሱቆቻቸውን እየዘጉና ሚኒባሶቻቸውን እያቆሙ ከነዚሁ መከረኞች ጋር ወደ አዲስ አበባ እየተሳፈሩና የመሳፈሪያ ጊዜያቸውን እየጠበቁ ነው፡፡ በየመንም ያሉት ኢትዮጵያዊያኑን ሲያሰቃዩ የነበሩት ኢትዮጵያዊያንም እንዲሁ፡፡ አገር ቤት ያሉት ደላሎችና ኤጀንሲዎች ባለ በርካታ ፎቆችና መኪኖች ባለቤት መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
ታዲያ እነዚህን ሁሉ ወንጀለኞች እያወቅናቸውና በመካከላችን አቅፈናቸው እየኖርን፣ ወገንን ለባርነትና እንደ መኪና መለዋለጫ አካላቸውን እየተተለተሉ በመቸብቸብ ንግድ ሀብትና ንብረት ያለማንም ከልካይ አፍርተው በእነዚህ ተበዳዮች አገር ሲንፈላሰሱ እያስተዋልን ‹‹ይኼ ነገር ገነ አይቀጥልም›› ብለን የምናስብ ከሆነ መቼም ምን እንደምንባል አላውቅም፡፡ እስኪ ለመሆኑ የትኛው ደላላ ወይም ኤጀንሲ ነው ለኮፍ ለኮፍ ሳይሆን ለተከሰተው የሕይወት መጥፋት፣ ያአካል መጉደልና ያአዕምሮ መታወክ ተመጣጣኝ ቅጣት የተቀጣና ተመጣጣኝ ካሳ የካሰ?
መቼም አንዱን ካንዱ ማበላለጥ ቢያስቸግርም እንደ ከብት ኢትዮጵያዊያን የተቸበቸቡባቸውና የታረዱባቸው የስደተኛ ንግድ ሸሪኮች ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ማወቅ ደግሞ ሐዘኑን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ከየመን በረሃዎች አንስቶ በሳዑዲ ዋና ዋና ከተሞች ድረስ የተዘረጋው የግፍ ንግድ ምንም እንኳን በየመናውያኑና በሳዑዲያውያኑ ቢመራም በየመን በረሃዎች ውስጥ የነበሩት ገራፊዎችና በየከተሞቹ የሚገኙት ገንዘብ አቀባባዮች ግን በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ፡፡
ምን ይኼ ብቻ? በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎችስ እነኚህን ተስፈኞች እየደለሉና እያባበሉ ወደ ሞት የነዷቸውስ እነማን ነበሩ? ‹‹የሌላ አገር ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ በየመንደሩ ገብቶ ዜጎችን ለስደት መለመለ›› ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም፡፡ በዚህ የምልመላ ሥራ ላይ ለመሳተፍ ደግሞ የግድ ባይሆንም የተመልማዩ ወገን አካባቢ ነዋሪ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች ለዘመናት ተለጥፈው ስናነባቸው የከረምናቸው ‹‹ወደ ዓረብ አገር በነፃ እንልካለን›› የሚሉት ማስታወቂያዎች እማኞች ናቸው፡፡
http://minilik-salsawi.blogspot.com/201 … st_13.html