ለባቡሩ የተሰራው ሲፈርስ ምን ይባላል?

Dawit Solomon
ለባቡሩ የተሰራው ሲፈርስ ምን ይባላል?
——————
የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ ያላመሰቃቀለው ህይወት የለም፡፡ያልፈረሰ መንገድ ቤት አይጠየቅም፡፡ታይተው ያልተጠገቡ መኪና የናፈቃቸው መንገዶች ፈርሰዋል ባቡሩ ሊመጣ ነው ተብለው፡፡ንግድ ቤቶች የስንት ቤተሰብ ማገር የነበሩ ከቦታቸው ተነቅለዋል፡፡ስለ ባቡሩ እንጂ ባቡሩ ስላፈናቀላቸው ቤተሰቦች ህይወት ማውራት‹‹ጸረ ልማትነት›› በመሆኑም ንግድ ቤቱ ሲፈርስ ህይወቱ እየፈረሰ እንደሆነ ተንታኝ የማያሻው አባወራ የሆዱን በሆዱ አድርጎ‹‹የልማቱ ደጋፊ ነኝ››ይለናል፡፡
ባቡሩ ያፈረሳቸውን ተሻግረን ስንመጣ ከላይ ለመጥቀስ ከሞከርኳቸው መፍረሶች ጋር የማይገናኝ የመንገድ መፍረስ እናገኛለን፡፡የባበሩ ሃዲድ መዘርጋት የጀመረበት ቦታ ነው፡፡እዚሁ ሸገር ጉምሩክ ፊት ለፊት የባቡር መንገዱን ከመኪና መንገድ የሚለይ ግድግዳ ሳትመለከቱ እንዳልቀራችሁ እገምታለሁ፡፡መከለያው ከሰው ቁመት አይተናነስም የጎን ርዝመቱም የት የሌለ ነው፡፡በሲሚንቶ የተሰራው መከለያ ጠንከር ብሎ የመኪና ግጭትን ተቋቁሞ የታለመለትን አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ ብዙ የህዝብ ገንዘብ ፈሶበታል፡፡
ቻይናዊው ኮንትራክተር አበሻውን ቡልዶዘር አሽከርካሪ በእጆቹ እየጠቆመ ቡልዶዘሩ የሲሚንቶው ክምር ላይ ወጣ፡፡በጠራራ ጸሐይ ግድግዳው ተደረመሰ፣ሹፌሩ አንዱን እየናደ ወደ ሌላኛው አመራ፡፡ምን ጥፋት እንደተገኘበት ባላውቅም ግድግዳው እንዲፈራርስ ተደረገ፡፡ሌሎቹ የፈረሱት ለባቡር ተብለው ነበር፡፡ይህ ግን ለባቡሩ ተብሎ የተሰራ በመሆኑ ለምን እንዲፈርስ እንደተደረገ ሊገባኝ አይችልም፡፡አስፈላጊ ሆኖ ባለመገኘቱ፣ግድግዳው በመጣመሙ፣ግድግዳው ሲሰራ የመንገዱ ውበት በመቀነሱ፣መንገዱ በመጥበቡ፣ብቻ እንዲፈርስ የተደረገው በሌላም ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
እንዴት ነው ነገሩ ግን መቼ ነው ሳንጀምር የምናስበው፣መቼ ነው ህዝብ ማክበር የምንጀምረው፣ምናልባት ይህ የኮንትራክተሮች ጉዳይ ነው ሊባል ይችላል፡፡ቢሆንስ እየሰሩ የሚያፈርሱ ከሆነ ጨረስን ያሉንን እንደማያፈርሱት አልያም ስህተት እንደማናገኝበት በምን ልናምናቸው ነው?