ኢህአዴግ ጸረ ህዝብነቷን ዳግም አስመስከረች

Getachew=Shiferaw-
በጧቱ ነበር ወደ ወሎ ሰፈር ለማቅናት መንገድ የጀመርኩት፡፡ መሃል ላይ አንድ ስልክ ደረሰኝ፡፡ ‹‹የሰማያዊ ፓር አመራሮችና አባላት ታግተዋል›› የሚል፡፡ ለማረጋገጥ ወደ ቢሮ መሄድ ነበረብኝ፡፡ ቢሮ ስደርስ የአካባቢው ሰዎች ሰብሰብ ሰብሰብ ብለው ስለ ታሳሪዎቹ፣ ሳውዲ ውስጥ ስለሚሰቃዩት ኢትዮጵያውያን፣ ስለሰላማዊ ሰልፉ ያወራሉ፡፡
በርካታ ፖሊሶች በቢሮው አካባቢ ተሰባስበዋል፡፡ ግቢው ውስጥ ግን ማንም የለም፡፡ ቢሮው በር ላይ ሳውዲ ውስጥ ለሚሰቃዩት ወገኖች በምልክትነት የተሰቀለው ጥቁር ምልክት እንዳልተነሳ ስመለከት ፖሊሶቹ ስለ ጉዳዩ እውቀት እንደሌላቸው ገባኝ፡፡ አመራቹን በአንዳች ነገር ከሰው ብቻ እርምጃ እንዲወስዱ ተነግሯቸዋል ማለት ነው፡፡
ከሰዎች መረጃ እያሰባሰብኩ እያለ ሌላ ስልክ ደረሰኝ፡፡ ‹‹ወደ ጃን ሜዳ ፖሊስ ጣቢያ ወስደዋቸዋል›› የሚል ነው፡፡ ወደዛው መሄድ አለብኝ፡፡ አንድ ጓደኛየን አግኝቸው ከእሱ ጋር አመራሁ፡፡ ኤምባሲው ጋር የሚደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ ለመቀላቀል እየረፈደብን ቢሆን ስለ ታሳሪዎቹ መረጃ ማግኘት ነበረብን፡፡
ጃን ሜዳ ፖሊስ ጣቢያ ስንደርስ ኢንጅነሩንና ሌሎች ጥቂት አመራሮችን ከርቀት አየናቸው፡፡ ሌሎቹን አስገብተው እየደበደቧቸውም ይሁን ለሌላ ጉዳይ ውስጥ ገብተው አይታዩም፡፡ ፖሊሶቹ ወደ እኛ ሲመጡ ሳውዲ ኤምባሲ ያለውን ጉዳይ ከመታሰር ብለን ታሳሪዎቹን ከእርቀት ሰላም ብለን ወደ ኤምባሲው እየተቻኮልን አቀናን፡፡
ሰዓቱ እየሄደ በመሆኑ ላንደርስ እንችላለን ብለን ሰግተናል፡፡ በእርግጥ የኢህአዴግ አንዱ ስልትም እንዲህ በተለያዩ ጉዳዮች በመወጠር ዋናውን ነገር ማሳት ነው፡፡ ወሎ ሰፈር አካባቢ ወደ 6 ሰዓት አካባ ስንደርስ ጥቁር የለበሱ ሰዎች ከኤምባሲው አቅጣጫ እየተመለሱ ነው፡፡ ሌላው ህዝብ ደግሞ በየ መንገዱ ዳር ቆሞ ይመለከታል፡፡
ይበልጥ እየቀረብን ስንሄድ የምናውቃቸውን ሰዎች አገኘን፡፡ እስካሁን አልተደበደብኩም የሚል ሰው አላጋጠመንም፡፡ አንዲት ምን አልባትም ሳውዲ ውስጥ የምታውቀው ሰው ጥቃት የደረሰበት ዘመድ ያላት የምትመስል ሴት ስቅስቀስ ብላ ታለቅሳለች፡፡ ሙሉ ጥቁር ልብስ ለብሳለች፡፡ ይህች ሴት እንዲህ የምታለቅሰው ከድብደባው ይልቅ ለዜቾቻችን ክብር ያልተሰጣቸው መሆኑ ነው፡፡
ሌላኛዋ ደግሞ የምታለቅሰው በጣም በመደብደቧ ነው፡፡ አንድ ሌላ ወጣት (ጓደኛየ ጋር ይተዋወቃሉ) ሰላም ካለን በኋላ በየ ቦታው ይቀመጣል፡፡ ምኑን እንደመቱት ስንጠይቀው ኩላሊቱ አካባቢ የተገመደለ አዲስ ቁስል አሳየን፡፡ ልጁ በንዴት ይቁነጠነጣል፡፡
በርካቶች መታሰራቸውን ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የነበሩት ነግረውናል፡፡ አብዛኛው የተበተነው ወጣት እያማረረ ነው፡፡ አንደኛው ‹‹ሰላማዊ ትግል አያስፈልግም›› ይላል፡፡ ለጎኑ ካሉት ክርክር ይገጥመዋል፡፡ ሌላኛው ‹‹ ነገ ኳስ ላይም ቢሆን ይህን ጮከታችን እናሰማለን››፣ ሌላኛው ‹‹እኔ የተደበደብኩት አገሬ ውስጥ ነው ወገኖቹ ሳውዲ ውስጥ እየሞቱ ነው፡፡››፣ ሌላኛዋ ‹‹እሁድም መጥተን መደብደብ አለብ›› ……
እኔም ቢሆን ኢህአዴግ ይፈቅዳል የሚል ተስፋ አልነበረኝም፡፡ ሰማያዊዮች ሲታሰሩም ማረጋገጥ የቻልኩት ይህን ነው፡፡ ግን መታሰርም ሆነ መደብደብ አንድ ነገር ነው፡፡ ይህ ለዜጎቻችንም ሆነ ለራሳችን ያለንን ክብር የምናሳይበት ነው፡፡ ኢህአዴግ ዳግመኛ ከገዳዮቻችን፣ ከጠላቶቻችን ጎን ቆሞ፡፡ ጸረ ህዝብነቱንም አስመሰከረ፡፡
አንዳንዴ ስትደበደብ ወይንም ስትሰታሰር ይወጣልሃል፡፡ እኔ እየዞርኩ ሳይ የዋልኩት የዜጎችን ሰቆቃ ብቻ ነው፡፡ እናም ቅጥል ብያለሁ፡፡